የኢንተርፕራይዞች ውጤታማነት ለአዲስ አበባ ብልፅግና !! " በሚል መሪ ቃልየአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ አስተዳደር ስራና ክህሎት ጽ/ቤት ነባር ኢንተርፕራይዞች በየዘርፉ የሚገጥማቸውን ማነቆዎች በመለየትና ባለድርሻ ተቋማትን በማሳተፍ ችግሮችን ለመፍታት ፤ ድጋፍ ለማድረግና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ በንግዱ ዘርፍ ከተሰማሩ ኢንተርፕራይዞች ጋር የውይይት መድረክ አካሄዷል። በውይይት መድረኩ የክፍለ ከተማው የስራና ክህሎት ጽ/ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ ዘነበ ወዬሳ በነባር ኢንተርፕራይዞች የድጋፍ ማዕቀፍና የባለድርሻ አካላት ሚና ላይ የተዘጋጀ የንቅናቄ ሰነድ አቅርበው ውይይት የተካሄደ ሲሆን በውይይቱ ኢንተርፕራይዞቹ የብድርና የገበያ ትስስር ችግሮች እየገጠሟቸው እንደሚገኝ ያነሱ ሲሆን የሚመለከታቸው አካላት ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተውባቸዋል። መንግስት በርካታ በጀትና ሀብት በማውጣት ኢንተርፕራይዞች የማቋቋምና በሙሉ አቅማቸው ወደ ስራ እንዲገቡ የመስሪያ ቦታ ከማመቻቸት ጀምሮ በርካታ ስራዎች እየተሰሩ እንደሚገኝ ያስታወሱት የክፍለ ከተማው ምክትል ዋና ስራ አስፈፃሚና የስራና ክህሎት ጽ/ቤት ኃላፊ ወ/ሮ ውቢት ዮሐንስ አስተዳደሩ በዘርፉ የተሰማሩ ኢንተርፕራይዞች የሚገጥሙ ተግዳሮቶችን ለመፍታት አስፈላጊው ድጋፍ ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን ተናግረዋል ። የክፍለ ከተማው የስራና ክህሎት ጽ/ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ ዘነበ ወዬሳ የንግድ ስራ ከትንሽ የሚጀመርና እየሰፉና እያደገ የሚሄድ ዘርፍ በመሆኑ መንግስት ባመቻቸው የብድር አገልግሎት በመጠቀም ጠንክሮ በመስራት ራስን መለወጥ መሸጋገር እንደሚገባ በማንሳት አስተዳደሩ ኢንተርፕራይዞች የሚያጋጥሟቸውን ተግዳሮቶች ለመፍታት ከባለድርሻ አካላት በቅንጅት የሚሰራ መሆኑን ተናግረዋል ።